የሲቪል ሰርቪስ ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጣቸው ጥራት በገለልተኛ አካል ሊመዘን እንደሚገባ ተጠቆመ

የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን እና የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድ ዛሬ በኮሚሽኑ አዳራሽ በተፈራረሙበት ወቅት የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ወ/ሮ ስመኝ ውቤ እንደገለፁት፣ የሲቪል ሰርቪስ መስሪያ ቤቶች የሚሰጡት አገልግሎት ጥራት በገለልተኛ አካል ተመዝኖ ሊረጋገጥ ይገባል፡፡

የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን በህግ በተሰጠው ተግባርና ኃላፊነት መሰረት መንግስታዊ አገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል የሚያስችሉ የተለያዩ ሥራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ የተናገሩት ምክትል ኮሚሽነሯ ጥራት ያለው፡ ተደራሽና ፈጣን መንግስታዊ አገልግሎት ለዜጎች መስጠት የሲቪል ሰርቪሱ ግደታ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡

በመሆኑም የሲቪል ሰርቪስ መስሪያ ቤቶች ይህን ግደታቸውን መወጣታቸው የሚረጋግጠው የአገልግሎት አሰጣጣቸው ጥራት በገለልተኛ አካል ተመዝኖ ሲረጋገጥ እንደሆነ አክለው የገለጹት ምክትል ኮሚሽነሯ፣ ይህም የምዘና ውጤቱን ተአማኒነት እንደሚያጎላው ገልጸዋል፡፡

የሲቪል ሰርቪስ መስሪያ ቤቶች የአገልግሎት አሰጣጣቸው ዜጎችን ያረካ እንዲሆን፣ ኮሚሽኑ ከኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት ጋር ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ በቅንጅት በመስራት ላይ እንደሚገኝም ጨምረው ያስታወቁት ምክትል ኮሚሽነሯ፣ ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጣቸውን ጥራት በዓለም አቀፍ የአገልግሎት አሰጣጥ የጥራት መለኪያ መስፈርቶች አስመዝነው በሚያገኙት የውጤት ግብረ-መልስ መሰረት ቀጣይነት ያለው የአገልግሎት አሰጣጥ መሻሻል ውስጥ እንዲገቡ የማድረግ ሥራ በጅምር ደረጃ እየተከናወነ እንደሆነ አብራርተዋል።

በጋራ ለመስራት የሚደረግን ይህን መሰል የስምምነት ፊርማ ጅምር አጠናክሮ በማስቀጠል የአገልግሎት አሰጣጥን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘና ጥራት ያለው የማድረጉ ጉዳይ የእያንዳንዱ መስሪያ ቤት ትኩረትና ተቋማዊ ባህል እንዲሆን እንደሚገባ ምክትል ኮሚሽነር ወ/ሮ ስመኝ አስገነዝበዋል፡፡ የእለቱ የስምምነት ፊርማ ስነ-ሥርዓትም አገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻያ ሥርዓት አንዱ አካል እንዲሆን ለማድረግ የታለመ ነው ሲሉም ገልፀዋል።

ተቋማትም የአገልግሎት አሰጣጣቸውን በማስመዘን በሚሰጣቸው ግብረ መልስ መሰረት ጥንካሬዎቻቸውን በማላቅ እና የጎደላቸውን እየሞሉ ቀጣይነት ያለው የአገልግሎት ጥራት መሻሻል በማምጣት ዜጋው የሚጠብቀውንና ከዚያም በላይ የላቀ አገልግሎት አሰጣጥ ውስጥ በመግባት ለዜጎች ጥራት ያለው አገልግሎት የመስጠት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ቴዎድሮስ መብራቱ በበኩላቸው ጥራት ሳይንስ በመሆኑ ዛሬ ዓለም በደረሰበት ደረጃ አገራት የኢንዱስትሪ ምርቶቻቸውን ውደ ገበያ በማውጣት ተወዳዳሪ የሆኑት ከጀርባቸው ሲቪል ሰርቪሱን አሰልፈው ነው ብለዋል።

የፌደራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ተቋማት አለም ዓቀፍ ስታንዳርዱን በጠበቀ መልኩ ገለልተኛ በሆነ ተቋም እንዲመዘኑና ደረጃ እንዲወጣላቸው ማድረጉ አገራዊ ኃላፊነት ካለበት ከአንድ ተቋም የሚጠበቅ ነው ሲሉም አክለው ገልፀዋል።

የውድድር ዋና ጥቅሙ የሲቪል ሰርቪስ ተቋማት ለዜጋው ጥራት ያለው አገልግሎት በሚሰጡበት ጊዜ የተረጋጋ ማህበረሰብ ይፈጠራል፤ ዜጋውም በመንግስት ላይ ያለው እምነት ይጨምራል ያሉት ዋና ስራ አስፈፃሚው፣ ድርጅታቸው ከፌደራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ጋር አብሮ ለመስራት ዝግጁ እንደሆነም ተናግረዋል።

የስምምነት ፊርማው በፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ወ/ሮ ስመኝ ውቤ እና በኢትዮጵያ ጥራት፣ ሽልማት ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ቴዎድሮስ መብራቱ መፈጸሙን ለማወቅ ተችሏል፡፡

 

Share this Post