“የሴቶች ተጠቃሚነት የሁሉም አጀንዳ ሊሆን ይገባል”
ወ/ሮ ስመኝ ውቤ የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ምክትል ኮሚሽነር
___________________________________________
የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ለተቋሙ አመራሮች በባለብዙ ዘርፍ አካታችነት በተለይም በስርዓተ ጾታ አካታችነት ዙሪያ ከሰኔ 11-12 2014 ዓ.ም ለኮሚሽኑ አመራሮች ሰልጠና እየሰጠ ነው፡፡
የሴቶች መለወጥ የሁሉም ማህበረሰብ መለወጥ መሆኑን የገለጹት የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ወ/ሮ ስመኝ ውቤ የሴቶችን ተጠቃሚነት ማሳደግ የሁሉም አጀንዳ ሊሆን ይገባል ያሉ ሲሆን የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ከ2.3 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የሀገሪቱ የመንግሰት ሰራተኞችን አዋጅ፣ መመሪያ እና የተለያዩ ሀገራዊ አቅጣጫዎች የሚያስፈጽም ተቋም እንደ መሆኑ ከኮሚሽኑ የሚወጡ መመሪያዎች እና አዋጆችም የሴቶችን ተጠቃሚነት ታሳቢ ያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በባለብዙ ዘርፍ አካታችነት በተለይም በስርዓተ ጾታ አካታችነት ዙሪያ ለኮሚሽኑ አመራሮች የተሻለ ግንዛቤን መፍጠርን ያለመው ስልጠና በኮሚሽኑ የሴቶች ህጻናት እና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት አማካኝነት የተዘጋጀ ሲሆን በስርዓተ- ጾታ አካታችነት ዙሪያ ሰፋ ያለ ገለጻና ማብራሪያ ከኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሰቲ በመጡት አዜብ አሰፋ (ዶ/ር) እና ወ/ሮ ሰብለ ሙሉጌታ ተሰጥቷል፡፡
በተለይም በስልጠናው የሥርዓተ-ፆታ አካታችነት ምንነት፣ ከአለም አቀፍ፣ከሀገር አቀፍ እና
በኮሚሽኑ ላይ ትኩረት ያደረጉ ገለጻዎች ቀርበዋል፡፡
የሥርዓተ-ፆታ ጉዳይን በሚወጡ ሀገራዊ ፖሊሲዎች፣ እቅዶች እና አጠቃላይ ሀገራዊ ፕሮግራሞች ማካተት በአጠቃላይ ሀገራችን እና ማህበረሰቡ ላይ የበለጠ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን በገለጻው ቀርቧል፡፡
የሥርዓተ-ፆታ ጉዳይን ቅድሚያ መስጠት በሴቶችም ሆነ በወንዶች ላይ ያሉ አሉታዊ ተጽእኖዎችን ከመቅረፍ ባሻገር በሴቶች እና በወንዶች ያለውን የተጠቃሚነት አለመመጣጠን በመለየት እኩል ተጠቃሚነት እንዲኖር ለማድረግ እንደሚያሰችልም ተገልጿል፡፡