ልዩ ነን እና ልዩ ስኬል የሚባል ጉዳይ በአዲሱ የሲቪል ሰርቪስ ስርዓት ቦታ የለውም”

የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ከኢ.ፌዲ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የሰው ሀብት ሥራ ስምሪት እና ቴክኖሎጅ ቋሚ ኮሚቴ እና ከሁሉም ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች እና ም/ሰብሳቢዎች ጋር በሲቪል ሰርቪስ ፍኖተ ካርታ፣ በፌዴራል የመንግስት ሰራተኞች አዋጅ፣ የመንግስት ሠራተኞች የሥራ መደቦች ምዘና፣ ደረጃዎች ምደባና የደመወዝ ስኬል ደንብ ዙሪያ እና አጠቃላይ የሲቪል ሰርቪሱ ቀጣይ ተግባራት ዙሪያ ሰፊ ውይይት አድርጓል፡፡

በውይይቱ ተገኝተው ገለጻና የመክፍቻ ንግግር ያደረጉት ኮሚሽነር መኩሪያ ሀይሌ (ዶ/ር) ኮሚሽኑ በአዲስ አመራር እና በአዲስ መንገድ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገልጸው የኮሚሽኑ ደንብም የሲቪል ሰርቪሱን ቀጣይ ተግባራት በሚያሳይ መልኩ በሚኒስትሮች ም/ቤት መጽደቁን ተናግረዋል ፡፡

ኮሚሽነሩ አክለውም የተቋማት አዲስ አደረጃጀትን ተከትሎ የተለያዩ የፌዴራል ተቋማት የመዋቅርና የአደረጃጀት ስራዎችን ሙሉ ጊዜ በመስጠት መሰራቱን የተናገሩ ሲሆን የዚህ መድረክ አላማም ኮሚሽኑ የጀመረውን አዲስ መንገድ ለሁሉም ቋሚ ኮሚቴዎች ግንዛቤ በመፍጠር በጋራ ለመስራት ያለመ ነው ብለዋል፡፡

የሲቪል ሰርቪሱን ተግባራት በውጤታማነት ለመፈጸም የሁሉም አካላት ርብርብ እንደሚያስፈልግ የጠቆሙት ኮሚሽነሩ አንዳአንድ ተቋማት የራሳቸውን ምክንያት በማቅረብ የልዩ ስኬል ጥያቄ እያቀረቡ መሆኑን ገልጸው ይሄ ጉዳይ በሲቪል ሰርቪሱ የደምዝና የክፍያ ስርዓት በመፈታቱ የልዩ ስኬል ጥያቄ ተገቢነት የሌለው መሆኑን በምትከታተሏቸው ተቋማት በማስረዳት በጋራ አብርን እንስራ ብለዋል፡:

በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የሰው ሀብት ስራ ስምሪት እና ቴክኖሎጅ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) በበኩላቸው የሲቪል ሰርቪሱ አጀንዳ የሁሉም አጀንዳ ነው ያሉ ሲሆን ኮሚሽኑ የጀመራቸውን ስራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ የቋሚ ኮሚቴው ድጋፍ እንደማይለየው ገልጸው ኮሚሽኑ የሚያወጣቸውን ህጎች እና መመሪያዎች መተግበር የሁሉም ፌዴራል ተቋማት ሀላፊነት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በአጠቃላይ በውይይቱ የሲቪል ሰርቪሱን ሚና ማሳደግ እንደሚገባ በለውጥ መሳሪያዎች ዙሪያ ያሉትን ችግሮች መቅርፍና ውጤታማነታቸውን ማረጋገጥ እንዲሁም የሰራተኛውን የኑሮ ሁኔታ ታሳቢ ያደረገ የክፍያና የማበረታቻ ስርዓት መዘርጋት እንዳለበት በተወያዮቹ ተነስተው ምክክር ተደርጎባቸዋል ፡፡

Share this Post