የብሔራዊ መታወቂያ እና የፌደራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የዲጂታል መታወቂያ መሰረታዊ የመንግስት ሰራተኛ መታወቂያ እንዲሆን የሚያስችል የስራ ስምምነት ተደረገ
በስምምነቱ ላይ ተገኝተው ማብራሪያ የሰጡት የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም የቴክኒክ ዳይሬክተር አቶ ዕዮብ ዓለሙ፤ የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም እና የፌደራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ያደረጉት ስምምነት የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ሠራተኞች አስተማመኝና ደህንነቱ የተጠበቀ የመታወቂያ ሥርዓት እንዲኖር ከማድረጉም ባሻገር አገልግሎትን በማዘመን ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት አስረድተዋል፡፡
ይህ የዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ የዲጂታል ትርንስፎርሜሽን 2025ን ለማሰካት ዋናውና አንዱ ምሰሶ ነው ያሉት አቶ እዮብ እያንዳንዱ ዜጋ ሕጋዊ በሆነ መንገድ ማንነቱ የሚረጋገጥበትና ከማንነት ጋር በተያያዘ የሚገጥሙ ችግሮችን በአስተማማኝ ሁኔታ የሚፈታ ነው ብለዋል፡፡ ከሰራተኞች ጋር በተያያዘም የያንዳንዱን ሠራተኛ የቅጥር ሁኔታ፣ የሥራ ታሪክና የሰነድ ማስረጃዎች ከዲጂታል መታወቂያ ጋር ከተያያዙ፣ የሰነድ ማጭበርበርን እና የሙስና ችግርን እንደሚቀርፉ አቶ እዮብ ገልጸዋል፡፡
የፌደራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን መረጃ ማደራጃ ዳይሬክተር ዶ/ር ብሩክ ይርጋ በበኩላቸው፡ ይህ ስምምነት እያንዳንዱ የሲቪል ሰርቪስ ሠራተኛ አስተማማኝ የማንነት መለያ ቁጥር እንዲኖረው ያደርጋል፤ የተሟላ መረጃን ወደ ብሔራዊ የመረጃ ቋት ለማስገባትም ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል፤ እንዲሁም ትክክለኛውን የሠራተኛ ቁጥር መረጃም ለማወቅ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ዜና የትምህርት ሚኒስቴር ከብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ጋር በመተባበር የዲጂታል መታወቂያ ስርዓትን መደበኛ የተማሪዎች መለያ አድርጎ ለመተግበር ከብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ጋር ስምምነት ላይ ደርሷል።ይህ ተነሳሽነት ኢትዮጵያ የትምህርት ዘርፉን ዲጂታል ለማድረግና ለማዘመን በምታደርገው ጉዞ ወሳኝ ስለመሆኑ መገለፁ ይታወሳል።